ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ ከ1500 በላይ የትወና ክህሎቱ ያላቸው ወጣቶችን ላለፉት ጥቂት ወራት በመመዘን በአዲስ ምዕራፍ ለሚጀምረው እና በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ላተረፈው የኛ አዳዲስ ተዋንያን በይፋ ተመርጠዋል።
አዲሶቹ ተዋንያን - አምስት ልጃገረዶች እና ሁለት ታዳጊ ወንዶች ሲሆኑ መረጣው የተካሄደው ባላቸው የትወና ብቃት፣ ለስራው ባላቸው ተነሳሽነት እና የየኛን እሴቶች ለመሸከም ባላቸው ስብዕና ነው። ገፀ-ባህርያቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ እና የተለያየ ማህበረሰብን እንዲወክሉ የተደረገ ሲሆን እንደቡድን በአንድ አይነት ስሜት የየኛ አምባሳደር በመሆን ለመስራት ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው ናቸው።
በአዲሶቹ ተዋንያኖች አዲሱ የየኛ ቴሌቪዥን ድራማ በመጋቢት ወር ለዕይታ የሚበቃ ሲሆን ሰባት ወጣት ኢትዮጵያውያን በየኛ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ የሚያደርጉትን የጓደኝነት ጉዞ ያስቃኘናል። ሰባቱ ተዋንያን ህልማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጉዞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ጉዞ የሚያፀንባርቅ ሲሆን ፀደንያ ለማ የዋኋ ፀጋን፣ብሌን አለም አሳቢዋ ሎሚን፣ ፅናት ተረፈ እንደ ደፋሯ አለም፣ ትርሃስ እንደ አመጸኛዋ ፍቅር፣ ቤተልሄም ሸፍረዲን እንደ ብልኋ ሃና፣አቤኔዘር ተስፋዬ እንደ ጉልበተኛው ዳዊት እንዲሁም ያሬድ አለማየሁ እንደ ተግባቢው ሃይሌ ሆኖ የሚጫወቱ ይሆናል።
ይህ ድራማ ዋና ግቡ በድራማው ላይ ተቀነባብረው የምናገኛቸው ምናባዊ ታሪኮች በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ታዳጊዎችን ውስብስብ ህይወት እንዲያሳይ እንዲሁም ገፀ-ባህርያቱ ለታዳጊዎቹ አርዓያ በመሆን ታዳጊ ሴቶች ፈተናዎችን እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ እንዲማሩባቸው በማሰብ ነው። የኛ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመርያ ታዳጊ ወጣቶችን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀ ድራማ ነው።
የኛ ለታዳጊ ወጣቶች እንደ መልዕክት ማስተላለፍያ መንገድ ድራማ እና ሙዚቃን በመጠቀም ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሴቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅም እንዲረዱ እና የሚገጥማቸውን ፈተና እንዲቋቋሙ ያግዛል። የኛ ድራማ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል ለ9 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾች በመድረስ ታዳጊ ሴቶች በኢትዮጵያ ስለሚኖራቸው ሚና ውይይቶችን በመፍጠር አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ችሏል።
9 ምዕራፍ ድረስ ከሄደ ተከታታይ የሬድዮ ድራማ እና 11 ምዕራፎች ከሄደ የሬድዬ ቶክ ሾው በኋላ የኛ ድራማን በቴሌቪዥን ይዞ መምጣት በመላው ኢትዮጵያ በታዳጊ ሴቶች ዙርያ የኛ የፈጠረውን ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይረዳዋል።