የመልካም ለውጥ ታሪክ
የኛ ከ2005 ዓም ጀምሮ ታዳጊ ወጣቶች በዋነኝነት ደግሞ ሴት ልጅአገረዶች ላይ አተኩሮ የሚሰራ እና በይዘታቸው ከበድ ያሉ ማሕበራዊ ጉዳዮችን ቀለል ባለ መልኩ በሬዲዮ ድራማ፥ የሬዲዮ ውይይት መድረኮች እንዲሁም ሙዚቃዎችን በመጠቀም ለዛ ባለው መልኩ የሚዳስስ ፕሮግራም ሲሆን በአማራ ክልል እና አበባ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
የየኛ ፕሮግራሞች የተዘጋጁት ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጅአገረዶችን በማወያየት በእለት ተለት ሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ፈተናዎች ከተረዳ እና ለይቶ ካወጣ በኋላ ነው። የኛ ካለፉት 7 አመታት ጀምሮ ብዙ አድማጮችን የደረሰ በይዘቱ እና አቀራረቡም "ኢትዮጲያዊ" የሆነ ፕሮግራም እንደሆነ በኩራት ተነግሮለታል።
የኛ አሁንም በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ አዎንታዊ ለውጦችን ማምጣት እየቀጠለ ሲሆን በቅርቡ ደሞ በአዳዲስ የቴሌቪዥን ድራማ ይዞ በመምጣት ይበልጥ ገንቢ የሆኑ ውይይቶችን እየጨመረ መጥቷል። አዲሱ "የኛ፡ የሁላችንም ታሪክ" የተሰኘው ድራማ በጥቅሉ፣ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ጥሩ ጓደኝነት በሚያፈሩ 5 ሴቶች እና 2 ወንዶች ታሪክ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ ሴቶቹ በአነቃቂዋ የሙዚቃ መምህርት ህይወት የሚመራውን የአርት ክለብ ይቀላቀላሉ፡፡ ታድያ በክለቡ በሚኖራቸው ምርጥ ቆይታ በመነሳሳት ባንድ ለመመስረት ሲወስኑ፣ ዳይሬክተር ሰብለ ከዚህ በፊት የነበረውን የየኛ ባንድ ስም በድጋሚ እንዲይዙ ታበረታታቸዋለች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ፣ ለሙዚቃ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር፣ ገጸባህሪያቶቹ፣ ጓደኝነት፤ ወኔ እና በእራስ መተማመንን ከማዳበራቸው ባሻገር፣ የየራሳቸውን ልዩ ማንነት ያገኛሉ፡፡
© 2025 Yegna. መብቶች ሁሉ በሕግ የተጠበቁ ናቸው
Girl Effect